ታሪክ፦ የአለመግባባቶች መንስዔ ወይንስ መፍትሄ?

ታሪክ፦ የአለመግባባቶች መንስዔ ወይንስ መፍትሄ?

By Bayisa Wak-Woya

በቅርቡ ዶ/ር ላሬቦ ከኢሳት ጋዜጤኛ ጋር ያደረጉትን ቃለመጠይቅ ካዳመጥኩ በኋላ ለብዙ ጊዜ በአእምሮዬ ይመላለስ የነበረና በጽሁፍ ለማስፈር በጊዜ እጥረት ምክንያት ተግባራዊ ለማድረግ ያልቻልኩትን ስለ “ታሪክ ምንነትና አስፈላጊነት” ዛሬ ጥሩ ሰበብ ሆኖኝ ይህን የግል አስተያየት ለመጻፍ ተነሳሁ። ዓላማዬ ዶ/ር ላሬቦ ስለ ኦሮሞዎች የተናገሩት ወይም ለማለት የፈለጉትን ጠቅሼ ለመውቀስ ሳይሆን እሳቸው ዋቢ አርገው ያቀረቡትን የዘመናት የኢትዮጵያን ታሪክን እንደ አንድ ኦሮሞ ምሁር በሌላ መነፅር ለማየትና አሁን ባገራችን በመከሰት ላይ ላለው አለመግባባቶች የሚያቀርቡት መፍትሄ ካለ ለማሳወቅ አለያም ሌላ አማራጭ ሃሳብ ለማቅረብ ነው። እግረ መንገዴን ግን ዛሬ ወገኖቻችን ከዳር እስከዳር በወያኔ የግፍ አገዛዝ ስር እየማቀቁ ሕፃን ዓዋቂ ሳይባል በጸጥታ ኃይሎች ጥይት እየጋዩና ይህንንም የግፍ አገዛዝ ገርስሶ ለመጣል የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን ለማጠንከር ቀና ደፋ በሚልበት ሰዓት ኢሳት ለምን በገንቢነቱ የማይታማውን የጥንት የኢትዮጵያ ታሪክ መፈተሽ አስፈለገው ስለሚለውና ፕሮፈሰሩም ቢሆኑ ካነጋገራቸው እንደተረዳሁት ከሆነ ስለ ኦሮሞ ሕዝብና ታሪክ ቀና አመለካከት ያላቸው ስላልመሰለኝ እንደሁ ጠቅለል ባለ መልኩ የበኩሌን አስተያየት ለመሰንዘር ፈለግሁ።

ወደ ዋናው አርዕስት ከመግባቴ በፊት ግን ዶክተሩ ስለ ኦሮሞ ሕዝብና ታሪክ ያላቸውን ግምት የተዛባ መስሎ ስለታየኝ ከወድሁ ባጭሩ ትንሽ መልዕክት አስተላልፌ ልሻገር። ዶክተር ላሬቦ በአገር አቀፍ ደረጃ አሉ ከሚባሉት የታሪክ ምሁራን አንዱ ቢሆኑም ትንሽ ምሁራዊ ቅንነት የጎደላቸው ይመስለኛል። አለበለዚያ ይህን ያህል ዓመት የምርምርና የማስተማር ልምድ ያላቸው የታሪክ ምሁር አንድ ሕዝብ መጠርያ ስሜ ኦሮሞ ነው ሲል አይ “አልስማማም” ማለት የቅንነት ማነስ እንጂ የእውቀት ማነስ አይመስለኝም። የአንድን ሕዝብ ይቅርና የአንድን ግለሰብ ስም እንኳ “አልስማማም” ለማለት የሚሞክር ሰው ጤንነቱ ራሱ አጠራጣሪ ነው። እኔ ዶከተር ላሬቦን አይ ላሬቦ አይደሉም ሌቦ ነዎት ካልኩ ወይ መሃይም ነኝ ወይም ደግሞ ዕብሪትና ማንአለብኝነት የተጠናወተኝ ነኝ። ከዚህ ውጪ ሌላ ምክንያት ሊኖርአይችልም።

ልጅ ሆኜ ስለ ዓለማችን ይቅርና ስለ አካባቢዬ እንኳ በውል በማላውቅበት ዘመን በቡና መከር ወቅት ከአዋሳኝ ክፍለ ሃገር ይመጡ የነበሩትን አማርኛ ተናጋሪ ወገኖቻችንን ራሳቸውን በሚጠሩበት ሳይሆን እኛ ያካባቢው ኦሮሞዎች ባወጣንላቸውና ኋላ እንደተረዳሁት ከሆነ በጣም አስጸያፊ ስም ነበር የምንጠራቸው። ዞር ብዬ ሳስታውሰው የያኔው አድራጎቴ በጣም ቢያሳፍረኝም መነሻው የዕውቀት እጥረት በመሆኑና ዛሬ ደግሞ ነገሮቹን ሁሉ በምሁር ዓይን ስለማይ ያንን የተሳሳተ ድርጊቴን አስተካክያለሁ። ለዕድገት በህብረት ዘመቻ ወደ አላባ ቁሊቶ ከመሄዴ በፊት “ጉዴላ” ማለት ለሃድያ ሕዝብ “ወላሞ” ደግሞ ለወላይታ ሕዝብ የተሰጠ አስፀያፊ ስም መሆኑን አላውቅም ነበር። ዛሬ ግን እነዚህን ጸያፍ አባባሎች ለዘላለሙ ከጭንቅላቴ ፍቄ ሕዝቦቹን በትክክለኛ ስማቸው እጠራቸዋለሁ። ዶክተር ላሬቦን ለማለት የፈለግሁት፤ ፈለጉም አልፈለጉም እኛ ራሳችንን የምንጠራው ኦሮሞ ብለን ነውና ራስዎን በማንአለብኝነት ከሚያስገምቱ  አቋምዎን አስተካክለው “ኦሮሞ” ብለው ቢጠሩን ይሻላል ባይ ነኝ። አሻፈረኝ ካሉ ደግሞ እዚያው በመረጡት የማንአለብኝነት ጎራ ውስጥ ይቅሩ – እኛ ግን ስማችንን አክብረው በስማችን ከሚጠሩን ወገኖቻችን ጋር በሰላም ጉዞአችንን እንቀጥላለን። ምርጫው የርስዎ ነው።

በነገራችን ላይ አንድ ሕዝብ የፈለገውን መጥፎ ወይም ጥሩ ስም መርጦ ለራሱ መጠርያ ሊያደርግ ይችላል። ያ የተመረጠው ስም ትርጉሙ ደስ የማይል እንኳ ሆኖ ቢገኝ ሕዝቡ ፈልጎ ተስማምቶበት እስካደረገ ድረስ  የህዝቡ መጠርያ ሆኖ ይቀራል። እስቲ ሁላችን የምንኮራበትና ዓለም ሁሉ እንዲያውቅልን የምንፈልገው “ኢትዮጵያዊ” እና “ሃበሻ” የሚሉትን ትንሽ ገባ ብለን ከምንጩ እንፈትሽ። የታሪክ ምሁር ባልሆንም እስካሁን በየቦታው ሲጻፍና ሲነገር እንደሰማሁት ከሆነ “ኢትዮጵያ” ማለት ግሪኮች ከሜድቴራንያን ባህር በስተደቡብ ለሚገኙት ጥቁር ሕዝቦች የሰጡት ስም ሲሆን ትርጉሙም “የተቃጠለ ፊት” ወይም “ጥቁር” ማለት ነው። ይህ እንግዲህ በዛሬው ቋንቋ “ኔግሮ” ወይም ደግሞ ዘረኛ ነጮች እንደሚሉት “ኒገር” ማለት ነው። “ሐበሻ” ማለት ደግሞ የዓረብኛ ቋንቋ “የተከለሰ/ክልስ” “ድብልቅ” ወይም “የተዳቀለ/ዲቃላ” ማለት ነው። ይህ እንግዲህ ትርጉሙን አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ወደን ተቀብለን የምንጠራበት ብቻ ሳይሆን በዓለም ሁሉ የምንኮራበት፤ ሰዎች ተሳስተው እንኳ በሌላ ስም ቢጠሩን በመናደድ ብዛት ጸጉራችን የሚቆም፤ በመጽሃፍ ቅዱስ እንኳ ደጋግሞ የተወሳ ቅዱስ ስም ነው ብለን ተቀብለን እንኖራለን። በካናቴራና መለዮአችን ላይ አንዳንዴም ነሸጥ ሲያደርገን በክንዳችንና ጡንቻችን ላይ ”ኩሩ ሃበሻ“ ”ኩሩ ኢትዮጵያዊ“ የሚል አስነቅሰን ደረታችንን ነፍተን እንንጎራደዳለን። ትክክለኛ ትርጉሙ “ኩሩ ዲቃላ” ወይም ” ኩሩ ጥቁር“ ማለት ቢሆንም ራሳችን ያለምንም ተፅዕኖ በፍላጎታችን የወሰድነው ስም ስለሆነ ብቸኛ መጠርያችን ነው። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ ይላል መጽሃፉ! ይህ ሁሉ እንግዲህ በቅንፍ ውስጥ ነው።

ወደ ዋናው ቁም ነገር ልመለስና ታሪክ ምንድነው? ማንስ ይፅፈዋል? የታሪክ መረጃዎች ትክክልነትስ ምን ያህል አስተማማኝ ነው? የታሪክ መረጃ ተብለው በጽሁፍም ሆነ በአፈ-ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተላልፎ  የደረሰንስ ዛሬ ላለንበት ሁኔታስ መፍትሄ ይሆናሉ ወይ? የተሰኙትን እስቲ ባጭሩ እንመልከት።

በግሌ ታሪክን እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ ከመጠን በላይ እወዳለሁ። ሕዝቦች እንዴት አብረው እንደኖሩ፤ የተፈጥሮ ችግርን እንዴት ተባብረው እንደፈቱና የጋራ ጠላትን እንዴት እንደተቋቋሙ ስለሚያስረዳ ታሪክ እውነትም አስፈላጊ ነው እላለሁ። ሆኖም ግን ምክንያቱን በውል ባላውቅም በኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንማር ከነበረው የታሪክ ትምህርት ”ዘመነ መሳፍንት“ የሚባለው ክፍል በጣም ይደብረኝ ነበር። ሌሎቹም ጓደኞቼ እንደማይወዱት አውቅ ነበር። ዛሬ በበሰለ አዕምሮ ዞር ብዬ ሳስተውለው የድብርቱ ምክንያት የታሪክ ሃተታዎቹ በሙሉ ይገልጹት የነበረው በየቦታው በነበሩ አለቆችና ገዢ ነን ባዮች መካከል ይካሄድ የነበረው ጦርነትና ጠላት ተብዬውን ለመጉዳት ይጠቀሙበት የነበረው ኢሰብአዊ ድርጊት በጣም የሚያሰቅቅ በመሆኑና በምንም መልኩ የዜጎችን መብትና ጥቅም ግምት ውስጥ ያላካተተ ስለነበር የመስለኛል። ኋላ ለማስረዳት እንደምሞክረው በግጭቶች ጊዜ የሚጻፉ ዜና መዋዕሎችን እንደ ትክክለኛ የዕውነትነት ማስረጃ አርጎ ማቅረብ ለብዙ አለመግባባቶችና ግጭቶች መንስዔ ነው ባይ ነኝ። እስቲ ላብራራ።

በጦርነቶች ጊዜ ወይንም እነሱን ተከትሎ የሚጻፍና የኋለኛው ትውልድም እንደ ታሪክ መረጃ አርጎ የሚጠቀምባቸው የጽሁፍ ቅርሶች ብዙውን ጊዜ በሁለት ነባራዊ ሁኔታዎች ይወሰናሉ። ሀ) መረጃዎቹ ወገናዊነት ስለሚያጠቃቸው ሁኔታውን በትክክል አያንጸባርቁም፤  ለ) ታሪክ ሁልጊዜ የድል አድራጊዎች ስለሆነ የተሸናፊ ታሪክ አይጻፍም፤ ለሕዝብም አይደርስም። ይህ እንግዲህ በጅምላው ሲታይ ነው፤ ጥልቅ ምርመራ ከተደረገ ግን ተጨማሪ ጉድለቶችም ይኖራሉ ብዬ እገምታለሁ።

ታሪክ ዘጋቢዎች በተለይም ግጭቶችን፤ ጦርነቶችን አስመልክተው የሚጽፉት ነባራዊውን ሁኔታ በትክክል ከመግለጽ የሚገድባቸው ሁለት መሰረታዊ ሃቆች አሉ። አንደኛ ማንኛውም ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ተፋላሚ ኃይሎቹ የተገኘውን ዘዴ ተጠቅመው ዕውነትን መገደል አለባቸው። ይህም ማለት ወደጦርነቱ የገፋፋቸው የተቃራኒው ወገን ”የተሳሳተ“ ”ሕጋዊ ያልሆነ“ የዚህኛውን ወገን ህልውና የሚጎዳ ድርጊት ነው ብለው በሃቅ ላይ ያልተመሰረተ ወሬ መንዛትና የሕዝቡን ድጋፍ ለማግኘት ቅስቀሳ ማካሄድ ነው። ጄነራል ኮሊን ፓወል በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት አዳራሽ ውስጥ ለዓለም ሕዝብ በአደባባይ ”ሳዳም ሁሴን ዓለምን ሊያጠፋበት ያዘጋጀው የጅምላ – አጥፊ መርዝ ነው ብለው ያሳዩት ትንሽ ብልቃጥ ዓይነት ማለት ነው። ለዚህም ነው “በግጭቶች ጊዜ የመጀመሪያው ሰለባ ዕውነት ነው” የሚባለው። ሁለተኛ እያንዳንዱ ተፋላሚ ወገን ተቃራኒውን እንደ ሰይጣን አርጎ ለሕዝቡ ማሳየት አለበት። አለበለዚያ ቀና ሰውን ለመውጋት እሄዳለሁ ብሎ መዘጋጀትም፤ ሕዝብንም ማስከተል አይቻልም። እነዚህ ሁለቱ ሲደመሩ፤ ማለትም ህዝቡ “ዕውነት” ነው ተብሎ የቀረበለትን “መረጃ” እና ተቃራኒው ወገን ከሰይጣን ያላነሰ  አጥፊ መሆኑን በቅድመ – ቅስቀሳው ሲያምንበት በሙሉ ልብ ዘምቶ ጦርነቱ ላይ ተካፍሎ ”ለዕውነትና” ወገኖቹን “ከአጥፊ ሰይጣን ለማዳን” ሲል ቆርጦ ይዋጋል ማለትነው።

እንግዲህ እያጠበብን እንሂድና፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ እስካዛሬ ስንማራቸው የነበረው የጦርነት ጊዜ ታሪኮች ከሞላ ጐደል ይህንን ዕውኔታ የሚያንጸባርቁ ናቸው። ራቅ ብለን ሳንሄድ እንደገና በቅንፍ ውስጥ፤ ይህን ከላይ ያልኳቸውን በጦርነት ጊዜ ሥራ ላይ ይውላሉ ስላልኳቸው ዕውኔታዎች አንድ በግሌ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ተካፋይ የሆንኩበትን ጦርነት ለምሳሌ ያህል ላቅርብና የውይይቴን ይዘትና አቋም ላጠናክር። ጊዜው በዘጠናዎቹ መጀመርያ ላይ ነበር፤ በምሥራቅና በመካከለኛው አውሮፓ መንግሥታት መካከል መለስተኛና አልፎ አልፎም የከረሩ የርስ በርስ ግጭቶች መካሄድ የጀመሩበት ጊዜ ነበር፤ ከነዚህ መሃል በዩጎዝላቪያ የተቀሰቀሰው ጦርነት የዓለም-ዓቀፍ ኅብረሰቡን ከሚገባ በላይ አሳስቦታል፤ በዚህ ጊዜ ነበር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተ.መ.ድ) እኔና አንድ ማይክል የተባለ አሜሪካዊ ለሥራ ተመድበን ወደ ዩጎዝላቪያ ያመራነው፤ ክሮኤሽያ ዋና ከተማ ዛግሬብ እንደደረስን የድርጅቱ ልዩ መልዕክተኛ እኔን ወደ ስፕሊት (የክሮኤሽያ ደቡብ ከተማ) ማይክልን ደግሞ ወደ ቤልግሬድ (የሴርብያ ዋና ከተማ) አሰማራን። ዓላማው ከተለያየ ቦታ ሆነን ክሮኤሽያና ሴርብያ በሁለቱ አገሮች መሃል በምትገኘው በቦስንያ ግዛት ላይ ያካሄዱት የነበረውን እጅግ በጣም አስከፊ የሆነው ጦርነት በሰላማዊው ሕዝብ ላይ ያደርስ የነበረውን ጉዳት በቅርብ ተገኝተን እንድንዘግብና ለተጠቂውም ሕዝብ አስፈላጊውን ቁሳቁሳዊና ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚገኝበትን ዘዴ ለመቀየስ ነበር። ሁለታችንም ተልዕኮአችንን በሚገባ ለመፈጸም በየቀኑ ድንበር እያቋረጥን ወደ ቦስንያ በመሻገር የተቻለንን ያህል ወደ ጦር ግንባሩ አካባቢ እየቀረብን “ከጠላት” ወገን በሚተኮሰው መድፍ ምን ያህል ንብረቶች እንደሚወድሙና ምን ያህል ሰላማዊ ሰው ለነፍሱ ፈርቶ ወደ ጎረቤት አገሮች እንደሚጎርፍ እንዘግብ ነበር። ታዲያ ካለሁበት ቦታ ሆኜ “የጠላትን” (ማለትም የሴርቦችን) አስከፊ ገጽታ በትክክል ለዓለም ሕዝብ ለመገለጽ ባይኔ ያየሁትን ብቻ ሳይሆን ከምረዳቸውም ሰላማዊ ሕዝቦች በቀጥታ የሰበሰብኩትን መረጃ አጠናቅሬ በየሳምንቱ ለልዩ መልዕክተኛው አስተላልፍ ነበር። ማይክልም ከቤልግሬድ በተመሳሳይ መልኩ “የጠላትን“ (ማለትም የክሮኤሽያዎችን) አስከፊ ድርጊት ከኔ በብዙ በተሻለ እንግሊዝኛ አጠናቅሮ ለልዩ መልዕክተኛው ይልካል። ልዩ መልዕክተኛውም የሁለታችንንም ሪፖርት ገለልተኛ በሆኑ ባለሙያዎች የተጻፈ መሆኑን በሙሉ ልቡ ስለሚያምንበት የንግግሩ ምንጭ አድርጎ ሳምንታዊውን ጋዜጣዊ መግለጫ ይስጥበታል፤ ከሱ በላይ የነበሩ የተመድ ባለሥልጣናትም የኛን ዘገባ እንደ ዋነኛ ምንጭ እንዲጠቀሙበት በየጊዜው ያስተላልፍላቸው ነበር።

የዩጎዝላቪያ የርስ በርስ ጦርነት ካለቀ ሃያ ዓመት የሞላው ሲሆን ያኔ እኔና ማይክል እንጽፋቸው የነበረው ሳምንታዊው የጦር ሜዳ ዘገባዎቻችን ቢያንስ ቢያንስ በተመድ ቤተመጻህፍት ውስጥ ይገኛሉ የሚል ግምት አለኝ። ታዲያ ዛሬ የዘጠናዎቹን የባልካን ጦርነት ለሚያጠኑና በዚሁ አርዕስት ላይ ቴሲሳቸውን ለሚጽፉ ወጣት የሴርብያና ክሮኤሽያ ዩኒቬርሲቲ ተማሪዎች የትኛውን ዘገባ ለዋቢነት እንደሚያቀርቡ መገመት አስቸጋሪ ይመስለኛል። ሆኖም ግን በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን ሽኩቻና መቆሳሰል በውል ስለማውቅ እነዚህ የዛሬዎቹ ወጣት ተመራማሪዎች ምን ዓይነት ድምዳሜ ላይ እንደሚደርሱ ከወዲሁ በዕርግጠኝነት ለመናገር እችላለሁ። ለሴርቡ ወጣት ገዝፎ የሚታየው የክሮአቶች “ሰይጣናዊ ተግባር” ሲሆን ለክሮአቱ ተመራማሪ ደግሞ ተቃራኒው ነው የሚታየው።

የምናወሳውና ሊከፋፍለን እንጂ ሊያስተባብረን ስላልቻለው ስለ ኢትዮጵያ የጦርነት ጊዜ ታሪክ ስለሆነ በዚህ የግል ታሪኬ አማካኝነት ምን ለማለት እንደፈለግሁ ይገባችኋል ብዬ እገምታለሁ። በኛና (እኔ ና ማይክልማለቴ ነው) የኢትዮጵያውን የጦርነት ታሪኮች ይዘግቡ በነበሩት ግለሰቦች መካከል ልዩነት ቢኖር የኢትዮጵያን የጦርነት ጊዜ ታሪክ ይጽፉ የነበሩት ዘጋቢዎች አንደኛ፤ እንደ እኔና ማይክል ገለልተኞች አልነበሩም፤ ሁለተኛ፤ ከሁለቱም ተፋላሚ ወገን ሁኔታዎችን ባንድ ጊዜ አጠናቅረው ለአንድ ገለልተኛ ለሆነ የበላይ አካል የሚያስተላልፉ አልነበሩም። ለዚህ ነው እንግዲህ “የኢትዮጵያ ታሪክ” ብለን ስንማር የነበረው ወገናዊ በሆኑ ጸሃፊዎች የተጠናቀሩና እንደሁ ገለልተኛ ሊሆኑ ይችላሉ ብለን እንኳ ብናስብ  በጦርነቶቹ ወቅት በሁለቱም ወገን ሊገኙ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር ባለመቻሉ ዘገባቸው ስለ አንዱ ወገን ብቻ ነው የምንለው። ሊዘግቡ የሚችሉትና በተግባርም እንዳየነው የራሳቸውን ወገን ገድል ብቻ ሲሆን ስለ ሌላው ወገን ግን የዘገቡትና “ለታሪክ ያቆዩት” ጭካኔያቸውን ብቻ ነው። አይፈረድባቸውም። በዓይናቸው ያዩት “ከጠላት ወገን” በሚተኮስባቸው ጥይት ወይም በተወረወረባቸው ጦርና ቀስት ሳቢያ በስቃይ ሕይወታቸው ያለፈውን “የወገንን ጦርና ባካባቢው ይገኝ የነበረውን ሰላማዊ ሕዝብ” ነውና! ልክ እኔ የሴርብያ መድፎች በክሮኤሽያና ቦስንያ ወታደሮችና ሰላማዊ ሕዝብ ላይ ያደርሱት የነበረው ጥፋት እንደዘገብሁ ማለት ነው።

ይህን ከላይ በተጨባጭ የሕይወት ማስረጃ እንደ አንድ ምሳሌ አድርጌ ያቀረብኩትን ወደ ኢትዮጵያ ዕውኔታ ስናመጣ ዘወትር ያለመግባባቶቻችን ሁሉ (በተለይም በኦሮሞና በአማርኛ ተናጋሪው ሕዝብ መካከል ያለውን) መገለጫው ምኒልክ ነው። ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ በኖረው የኦሮሞ አፍአዊ ታሪክ መሰረት እኚህ የሸዋ ንጉሥ ከፊንፊኔ በታች ያለውን የዛሬይቷን ኢትዮጵያ ግዛት በአንድ ማዕከላዊ መንግስት ስር ለማጠቃለል ባደረጓቸው ጦርነቶች ሁሉ እጅግ አሰቃቂ የሆኑ ግፎችን በሰላማዊው የኦሮሞ  ሕዝብ ላይ ፈጽመዋል፤ የጎልማሳ ወንዶችን ቀኝ እጅና የሴቶቹን ጡት ይቆርጡ ነበር፤ ሌላም ሌላም አስከፊ ድርጊቶቹ በአያቶቻችንና አባቶቻችን አፍአዊ ታሪክ በኩል ተላልፎልናል። ስለዚህ እኛ ኦሮሞዎች ስለ ዓፄ ምኒልክ ያለን ሥዕላዊ ግምት አንድ በሰው መልክ የተፈጠረ፤ ግን ቀንድ አይኑረው እንጂ ሥራው ሁሉ ሳጥናዔላዊ የሆነ የኦሮሞን ሰላማዊ ሕዝብ ፈጅቶ መሬታቸውን እንደቀማ ክፉ ፍጥረት ነዉ። ይህ እንግዲህ የኦሮሞ ሕዝብ በጠቅላላ ለዘመናት ያምንበት የነበረና ዛሬም ቢሆን ትክክለኝነቱ በምንም መልኩ ጥያቄ ውስጥ የማይገባ እንደ መጽሓፍ ቅዱስ በሙሉ ዕምነት በሰውነታችን የተሰረፀ ስለሆነ እንኳን በተራ ንትርክና ያገሪቷን እንዶድ በሙሉ ሰብስበን ብንጠቀም እንኳ ለማፅዳት የምንችል አይመስለኝም። በአንጻሩ ደግሞ አብዛኛው አማርኛ ተናጋሪ የሆኑ ወገኖቻችን – ዓፄ ምኒልክ ዘመናዊቷን ኢትዮጵያ የመሰረቱ፤ በዓድዋ ጣሊያንን ድል በማድረጋቸው ለጥቁር ሕዝብ የነፃነት ትግል ምሳሌና ተስፋ የነበሩ ታላቅ ሰው ናቸው ብለው ያምናሉ። በቴዲ አፍሮ “ምኒልክ ጥቁር ሰው” በሚለው ዘፈኑ በፊንፊኔ ትላልቅ ሆቴሎች ሠርግና ምላሽ ተደርጎ እስክስታ ሲወረድበት ይህንኑ ዘፈን ቃላቱን ቀይሮ “Miniilik nuuf diina” ብሎ ሹክሪ ጃማል በሚያቀነቅነውና “Miniilik bineensa” ብሎ ቀመር ዩሱፍ በሚያዜመው ደግሞ በሚኔሶታና በስቶክሆልም የሚገኙ ኦሮሞዎች ድል ያለ ድግሥ አዘጋጅተው ላባቸው እስኪንቆረቆርና ዘጠነኛው ዳመና ውስጥ የገቡ እስኪመስላቸው ድረስ ረገዳውን ይሉታል።

ነገርን ነገር ያመጣዋል እንዲሉ አንድ ጓደኛዬ የአርሲ ሕዝብ የምኒልክ “ጠላትነት” እንዴት ሰርፆ እንደገባባቸው የሚገልፅ ዕውነተኛ ታሪክ ነው ብሎ የነገረኝን ላጫውታችሁ። ታሪኩ አንድ የአሰላ ከተማ ኗሪ ኦሮሞ ወጣት ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቦ ዳኛው ላቀረቡለት የመግቢያ ጥያቄ የሰጠውን መልስ ነው።

ዳኛ፡     ስምህ ማነው?
ተከሳሽ፡           ገነሞ
ዳኛ፡     ዕድሜህ ስንት ነው?
ተከሳሽ፡            ዕድሜዬን አላውቅም ጌታዬ
ዳኛ፡     በጠላት ጊዜ ዕድሜህ ስንት ነበር?
ተከሳሽ፡           በጠላት ጊዜማ እንኳን እኔ አባቴም አልተወለደም
ዳኛ፡     ምንድነው የምታወራው? ጣሊያን ኢትዮጵያን ሲወር አባትህ አልተወለደም ነው የምትለኝ?
ተከሳሽ፡           ይቅርታ ጌታዬ ጠላት ሲሉኝ ስለ ምኒልክ የጠየቁኝ መስሎኝ ነው። አለ አለኝ።

ይህ እንግዲህ ስለ አንድ ምኒልክ፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለሳቸው ካላቸው ፍቅር የተነሳ “እምዬ” ብለው የሚጠሯቸውና “ቢቆርጡኝም ቢገድሉኝም ይሄው ቆምኩልዎ፤ ያለም ጣም ምኒልክ ብዬ ሰደብኩዎ” ተብሎ የተቀኘላቸው እንኳን ለኢትዮጵያ ይቅርና ለዓለም ሁሉ ጣዕም ናቸው የተባለላቸው ያገር መሪ ሁለት የተለያየ ታሪክ በመነገሩና ታሪኮቹን ተከትሎ ሁለት የተለያየና ተቃራኒ የሆነ አስተሳሰብ በኦሮሞዎችና በአማርኛ ተናጋሪ ሕዝቦች መካከል በመፈጠሩ ነው።

እንደዚህ ዓይነት የታሪክ ቅርሶችን ናቸው ብለን አምነን የተቀበልናቸውን የጽሁፍና የቃል መረጃዎችን ይዘን ነው እንግዲህ ለዓመታት ያህል እንደ ዋቢ አርገን በየፊናችን አንዱ ሌላውን ለማሳመን ብለን ስንናቆር የነበረው። የሚያሳዝነው ግን ዛሬም ከብዙ ዓመታት ንትርክ በኋላ ሁለቱም ወገን በአቋሙ ጸንቶ “እኔ የማምንበት ታሪክ በጽሁፍ የተደገፈ መረጃ ስላለው እንደ ብቸኛ የታሪክ ምንጭ መታየት አለበት” ሲል ሌላው ደግሞ “በወገናዊነት መንፈስ ከተጻፈው ካንተ የጽሑፍ መረጃ ይልቅ የኔ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረውና በጥንቃቄ ተይዞ እኔ ጋ የደረሰው አፍአዊ ታሪክ ትክክለኛ ነው” እያለ  ጉዞ ቀጥሏል። ለኦሮሞዎች ተፈጽሞብናል የሚሉት በደል ዝርዝር አንድን ነጭ ዝሆን ብርሃን በተሞላበት ቤት መሃል ላይ የቆመ ያህል በግልጽ ሲታያቸው በደሉ በጭራሽ አልነበረም የሚሉት ደግሞ በጨለማ ቤት ውስጥ ጥቁር ድመትን እንደመፈለግ ያህል ለማየት ከባድ ሆኖባቸዋል። በሌላ አነጋገር ሁለቱም ወገን በአቋማቸው የጸኑ በምንም ተዓምር የሌላውን ወገን መረጃ  ላለመቀበል ቁርጠኛ ውሳኔ  ላይ የደረሱ ስለሆነ እንዴት ነው እንግዲህ የእነዚህን ሁለት በጣም ተቃራኒ የሆኑ ሃሳብ አራማጆችን ባንድ መድረክ ላይ አምጥቶ በቀናነት ማወያየት የሚቻለው? በምንስ መለኪያ ለክተን ነው ይህኛው ታሪክ ትክክል ነው ይህኛው ግን ትክክለኛ አይደለም ለማለት የምንችለው? ባጠቃላይ እንዴትስ አድርገን ነው የነበሩትንና አሁንም በሕዝቦች መካከል ያለውን ግኑኝነት እያሻከሩ ያሉትን አለመግባባቶች በማስወግድ ካለንበት የፖለቲካ ቀውስ ወጥተን እርስ በርስ በመተማመን አዲሲቷን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በጋራ ልንገነባ የምንችለው? የሚለው እንቆቅልሽ መልስ አጥቶ ቀርቷል።

በኔ ግምት በቅርጽም ሆነ በይዘታቸው የተለያዩ ግን ደግሞ አሁን ካለንበት ያለመተማመን ሕይወት ውስጥ አውጥተውን አብሮ ወደ መጓዙ ዓለም ሊወስዱን ይችላሉ ብዬ ያሰብኳቸው ሁለት መንገዶች ይታዩኛል። ሁለቱንም እስካሁን ያልሞከርናቸው ስለሆነ ሊያዋጡ ይችላሉ የሚል ሙሉ ዕምነት አለኝ። ሁለቱን መንገዶች በደረጃ ከፍለን የመጀመርያውን ከሞከርንና አላዋጣ ካለን ወደ ሁለተኛው እንሻገራለን ማለት ነው። (ሁለቱም ተሞክሮዎች ከከሸፉ ግን ጉዳዩን ለአንድዬ አስረክቦ ወደ ለመድነው የአለመደማመጥና አለመግባባት አዟሪት ከመመለስ ሌላ ምርጫ ያለን አይመስለኝም)።

አንደኛው አማራጭ፤ ችግሩ አያትና ቅድመ አያቶቻችን በፅሁፍም ሆነ በቃል ባወረሱን መረጃ ላይ ያለመተማመን ጉዳይ ስለሆነ እስቲ ሌላ ያልተሄደበት መንገድ ያልተሞከረ ሃሳብ እንፈልግ የሚለው ነው። ለዘላለም መልሶ መላልሶ ያንኑ ውጤት-አልባ የሆነውን ሃሳብ ማቅረብ ዕብደት ነው። በመሆኑም እነዚህን ያልሄድንባቸውን መንገዶች ስፈልግ የታየኝ አንድ ሃሳብ፤ ለምን ሁለታችንም በዕድሜያችን ዘመን ያየነውንና በራሳችን ላይ የደረሰብን ወይም ባካባቢያችን ሲፈጸም ባይናችን ያየነውን “በደል” ብለን የመዘገብናቸውን ጭቆና ማስረጃ የሚሆነንን ተጨባጭ ድርጊት ለሕዝባችን የአዕምሮ ፍርድ ቤት አቅርበን ላንዴና ለመጨረሻ ተማምነን አዲስ የታሪክ መፅሃፍ ገጽ በመክፈት ሰላማዊ ጉዞ አንቀጥልም የሚል ነበር። ዓላማው በዳይና ተበዳይን ለይቶ ካሳ ለመክፈል ወይም ለመቀበል ወይም “ይቅርታ” ለማስጠየቅ ሳይሆን በመጀመርያ ደረጃ በደል እንደነበረ ለመተማመንና ቀጥሎ ደግሞ የተሰራው በደል በሕዝቦች መካከል ፍቅርን የማያዳብርና ጎጂ በመሆኑ ለወደፊት እንዳይደገም ጥሩ ትምህርት ይሰጣል ከሚል አንፃር ነው። መቼም ለሰው ልጆች ሌላውን ሰው መበደልን አምኖ መቀበል በመርፌ ቀዳዳ ውስጥ የማለፍን ያህል ከባድ ቢሆንም ድንገት ግን ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም አንዳንድ ቀና አስተሳሰብ ያላቸው ከህብረተሰቡ መሃል አይጠፉምና መሞከሩ ያዋጣል ባይ ነኝ። በሌላው ዓለም በእንግሊዝኛ truce and reconciliation የሚሉት ዓይነት መሆኑ ነው።

ከወዲሁ ግን እንዲታወቅልኝ የምፈልገው ሌላ ነገር ደግሞ እኔም ሆንኩ ሌሎች የኦሮሞ ምሁራን ስለ ብሄር ጭቆናና ጨቋኞች ስናወራ የዚያ የጭቆና ሥርዓት መደብ ተጠቃሚ የሆኑትን ባብላጫው የአማርኛ ተናጋሪ የሆኑትን የመደቡን አባላት እንጂ የአማራን ሕዝብ አለመሆኑን ለማሳሰብ እሻለሁ። ምኒልክ ከሸዋ መኳንንት ጋር ከመቅደላ አምልጦ ሲሸሽ ወሎ ላይ ተቀብላ አሳርፋ የራሷን ከመቶ ያላነሱ ኦሮሞ ጎበዞች ሰጥታው ወደ አባቱ አገር ወደ ሸዋ የላከችው የወሎዋ የኦሮሞ ንግሥት ወርቂቱ ነበረች። የራሱ ሥጋ ዘመዶች እንኳ መልሰን አናስገባውም ብለው መንገዱን ሲዘጉበት ወደ አባቱ አገር አንኮበርም አብረው ተዋግተው ለአባቱ መንበር ያደረሱት የልጅነት ጓደኞቹ እነ ጎባና እና ሌሎች ኦሮሞ ጎበዞች ነበሩ። የመጨረሻው የአማራውን ገዢ መደብ ሥርዓት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በበላይነት የመራው ዓፄ ኃይለሥላሴ ባባቱም (ደጃዝማች መኮንን ጉዲሳ የሸዋው ኦሮሞ ልጅ) በናቱም (ወይዘሮ የሺቤት ዓሊ ጂፋር የወሎው ኦሮሞ ባላባት) ኦሮሞ ነበሩ። ስለ ብሄር ጭቆና ስናወራ ችግሩ የነበረው በጨቋኙ ሥርዓት እንጂ በአማራና በኦሮሞ ሕዝብ መካከል እንዳልሆነ ለመድገም ያህል ነው። የዚህ የጨቋኙ ሥርዓት ተጠቃሚዎች አማርኛ ተናጋሪ ከመሆናቸው ሌላ የአማራውን ህዝብንም አይወክሉምም፤ ከበዘበዟቸው ሕዝብ የዘረፉትንም ሃብት ለአማራው ሕዝብ አላካፈሉም። በቋንቋ አጠቃቀምና በባህል ዙርያ የአማራ ገዢ መደብ አማርኛ ተናጋሪውን ሕዝብ የተሻለ ተጠቃሚ አደረገው እንጂ ድህነቱንማ (መደብ ጭቆናውን ማለቴ ነው) ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄርና ብብሄረሰቦች ለእኩል ነበር የተካፈሉት።

በዚህ ከተስማማን እንግዲህ ልቀጥል። በቅንፍ ግን አንድ ዓቢይ ጉዳይን ባጭሩም ቢሆን ለመግለፅ እሻለሁ፤  የምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጊዜ ታሪክ ከውይይታችን ክልል ውጪ ማድረጌ እስካሁን ድረስ በዚያ አካባቢ የተደረጉት ውይይቶች የባሰ መከፋፈልን እንጂ መቀራረብን ስላላስከተሉ ስልቱን በመቀየር ያልተሄደበትን መንገድ ለመሞከር እንጂ ታሪክ እንዲረሳ ለመገፋፋት አይደለም። እኔ ታሪክን እንድናስታውሰው የምፈልገው ለሰው ልጆች በሰላምና በፍቅር አንዱ የሌላውን መብት ሳይጋፋ በእኩልነት ለመኖር የሚረዳውን በጎ በጎውን ክፍል እየወሰድን ለዚህ ተጻራሪ የሆኑትን ድርጊቶች ደግሞ ስህተት መሆናቸውን አውቀን እንድናስወግዳቸው ከሚለው ሃሳብ ተነስቼ ነው።

ከሳሽ ስለሆንኩ እንግዲህ በተስማማነው መሰረት ሁለት የበደል ክሶቼን ብቻ ለሙከራ ያህል ላቅርብና እሰጥ አገባ እንጀምር።

ሀ) የአማራው ገዢ መደብ ሥርዓት ዋነኛ ተጠቃሚና የአገሪቷን ፖለቲካና ምጣኔ ሃብት ይቆጣጠሩ የነበሩት በአብላጫው አማርኛ ተናጋሪ የሆኑ ግለሰቦች የኦሮሞን ሕዝብ ከገዛ መሬቱና ቤቱ አፈናቅለዋል። የኦሮሞን ሕዝብ ከሞላ ጎደል ከባለመሬትነት ወደ ገባርነት ቀይረውታል፤ ውጤቱ፤  ጠቅላላው ቤተሰብ ይራባል፤ ይጎሳቆላል፤ ለበሽታና ብሎም ለሞት ይጋለጣል፤ ልጆቻቸውን ማስተማር አይችሉም፤  ለአዕምሮ ድህነት ይዳረጋሉ። ዘጠና ከመቶ በላይ ሕዝቡ በእርሻ በሚተዳደርበት አገርና ብቸኛ የማምረቻ መሳርያ የሆነውን መሬትን ከአራሹ የኦሮሞ ሕዝብ መንጠቅ ማለት በሕዝቡ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀልን እንደመፈፀም ነው ባይ ነኝ። በተቃራኒው በነዚህ ስድሳ ዓመታት ጊዜ ውስጥ የኦሮሞ ሕዝብ በቡድንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ወደ አማርኛ ተናጋሪው ወገኖቻችን ግዛት ሄዶ ከቄዬያቸው አፈናቅሎ መሬታቸውን የወሰደበት ጊዜ አልነበረም።

ለ) የአማራው ገዢ መደብ ሥርዓት ባወጣው ሕግ መሰረት ማንኛውም ተማሪ በአማርኛ ቋንቋ አጥጋቢ ውጤት ካላመጣ ዩኒቬርሲቲ መግባት አይችልም ነበር። በዚህም ምክንያት እጅግ በጣም ብዙ ኦሮሞ ልጆች በተለይም በገጠር አካባቢ ያደጉ ልጆች በሌላው ሁሉ የትምህርት ዘርፍ የላቀ ውጤት እያመጡ በአማርኛ ቋንቋ ያነሰ ውጤት በማምጣታቸው ብቻ የዕውቀት በሩ ለዘላለም ተዘግቶባቸዋል። ይህ እንግዲህ በዓይኔ ያየሁት በብዙ ጓደኞቸ ላይ የደረሰ ከፍተኛ በደል ነበር። በተቃራኒው ግን አማርኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ለሆነ ወገኖቻችን በሌላው የትምህርት ዘርፍ አጥጋቢ ውጤት እስካመጡ ድረስ በአማርኛ ቋንቋ ምክንያት የዩኒቬርሲቲው በር አልተዘጋባቸውም።

እንግዲህ የብሄር ጭቆናው አልነበረም የኦሮሞ ሕዝብም አልተጨቆነም የምትሉ ወገኖቼ ደግሞ በበኩላችሁ ባለፈው ሃማሳ ወይም ስድሳ ዓመት የዕድሜያችን ክልል ውስጥ የአማርኛ ተናጋሪው ሕዝብ የብሄር ጭቆና ደርሶበታል በዓይናችን አይተናል የምትሉትን ተጨባጭ የሆነ የጭቆና መገለጫ ይንገሩኝ። ከሌላችሁና እኔን ግን ካመናችሁኝ ዓላማዬ ግቡን መታ ማለት ነውና ይህንን የታሪክ ምዕራፍ ዘግተን ነገሮቹን ሁሉ ለታሪክ ማስታወሻነት አስቀምጠን ካሁን በኋላ እንዴት በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ማንም ማንን የማይጨቁንበትና ሁላችንም በሰላምና በፍቅር የምንኖርበትን የጋራ ቤት እንመሥርት ወደሚለው ገንቢ ውይይት እንሻገራለን ማለት ነው።

ሁለተኛው አማራጭ (ይህ በመጀመርያ ደረጃ  ያስቀመጥሁት ካልተሳካ ማለት ነው) ሁላችንም ላለመሰማማትና ላለመግባባት ዓምላካችን ልዩ አርጎ የፈጠረን ስለሆንን እንደው እንደ ሁለት የምልክት ቋንቋ እንኳ እንደማይችሉ ዱዳዎች ነጋም ጠባም ከመናቆር ሁላችንም የምናምንበትን እንዳመንንበት አቅፈን ላለመተማመን ደግሞ ተማምነን ላለመስማማት ተስማምተን የየራሳችንን ዘውድ እንደጫንን ዳግመኛ ግን ጉዳዩን አንስተን ሌላውን ወገን ለማሳመን መሞከር ማለት ጥቁር ወተትን ወይም ነጭ ኑግን የመፈለግ ያህል ከባድ መሆኑን ተገንዝበን አዲሲቷን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንዴት አብረን እንገንባት ወደሚለው ውይይት እናምራ። ይህ እንግዲህ “ሰውን ውደደው እንጂ አትመነው” የሚለውን ፊዉዳላዊ አስተሳሰብ ትተን “ሰውን ውደደው፤ እመነውም” በተባለው እምነት እንመራ ማለት ነው።

መደምደምያ

ዛሬ አገራችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የዜጎቿ መብት የተረገጠባት በታሪኳ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅበት ደረጃ ግድያና የእስር ቤት ስቃይ የተንሰራፋባት ብትሆንም በአንፃሩ ግን የተለያዩ ያገሪቷ ብሄርና ብሄረሰቦች ከመቼውም ጊዜ በላይ ልብ ለልብ ተናበው ይህንን ወገን ሳይለይ በጅምላ የሚበድላቸውን የወያኔን መንግሥት ገርስሶ ለመጣል ባንድ ላይ ተነስተዋል። ምንም እንኳ በመካሄድ ላይ ያሉት ሕዝባዊ ዓመፆች በደንብ በተደራጀ መልክና በአንድ ማዕከላዊ የፖለቲካ ድርጅት ባይመሩም፤ በቁርጠኝነት በመታገላቸው ብቻ የወያኔውን መንግሥት ኃይል እያዳከሙ ነው። በጎንደርና ባህር ዳር ለሰላማዊ ሰልፍ የሚወጣው የአማራ ሕዝብ “የኦሮሞን ሕዝብ መብት መግፈፍ የአማራን ሕዝብ መብት መግፈፍ ማለት ነው” የሚል መፈክር ሲያነግቡ የኦሮሞ ሕዝብ ደግሞ በዓፀፋው “የአማራ ሕዝብ ወንድማችን ነው” በማለታቸው ከዳር እስከዳር በተቀጣጠለው የኦሮሞ ሕዝባዊ ዓመፅ ጊዜ በክልሉ በሚኖሩ በሚሊዮን በሚቆጠሩ የአማራ ሕዝቦች ሕይወትና ንብረት ላይ አንዳችም አደጋ እንዳይደርስ ብርቱ ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር። ይህ ዕውኔታ እየተከሰተ ያለው  እኛ “ተማርን” የምንለው የኅብረተሰቡ ክፍል በዚህ ከወያኔ ሰይፍ ርቀን በምቾት ከምንኖርበት ውጭ አገር አንዳች እንኳ ሕዝባችንን የሚያቀራርብ ገንቢ ሃሳብ ማፍለቅ ባልቻልንበት ጊዜ ነው። በሕዝባችን ላይ የተመዘዘውን የወያኔን ገዳይ ጎራዴ መመከት የሚቻለው ደግሞ በተባበረ የኢትዮጵያ  ሕዝቦች ክንድ ብቻ ስለሆነ ባሁኑ ሰዓት የኛ የተማርን ባዮች የጋራ መፍትሄ መፈለግ  የውዴታ ሳይሆን የግዴታ ይመስለኛል።

ወገኖቼ! ማንኛችንም ቢሆን የተፈጥሮ  አጋጣሚ ሆኖ ነው እንጂ ፈልገን ወይም ታግለን አይደለም ኦሮሞ  ወይም አማራ የሆንነው። ያም በመሆኑ አባቶቻችንና አያቶቻችን ፈጽመዋል ለተባለው በደል እኛ አሁን ያለነው ትውልድ ተጠያቂ የምንሆንበት ምክንያት የለም። ሆኖም ግን ሁላችንም ኢትዮጵያ በተባለችዋ የጋራ አገር በሰላም ለመኖር እንመኛለን፤ ሁላችንም ቤተሰብ አፍርተን ልጆቻችንም ያለምንም አድልዎ በእኩልነት የሚያድጉባትን ዲሞክራሲያዊት አገር ለመገንባት እንፈልጋለን። ስለዚህ ቅንነት በተሞላበት መንፈስ ተቀራርበን ካላወራንና የወደፊት ጉዞአችንን ለመጀመር ካሁኑ ስንቅ ማዘጋጀት ካልጀመርን ሥልጣን ላይ ያለው የወያኔ መንግስትም አዝማሚያውን አይቶ ለጉዞአችን የምንፈልገውን ስንቅ እንኳ የፓርቲው አባል ካልሆናችሁ አልሰጣችሁም ብሎ ጉዞአችንን ሊያሰናክልብን ይችላልና በጥብቅ እናስብበት ባይ ነኝ። ይህ ቀጠሮ የማይሰጠው አጣዳፊ ጉዳይ በመሆኑ ስላለፈው ታሪክ ስንነታረክ የወደፊቱን ከነጭራሹ እንዳናጣ ዛሬ ባንድ ላይ ሆነን የነገዋን ዴሞክራሲያዊቷን ኢትዮጵያን ለመገንባት ያለ የሌለ ኃይላችንን አስተባብረን ሲሚንቶና አሸዋውን ማቡካት እንጀምር። ፈረንጆች “ዛሬ ወይም ምንም ጊዜ” የሚሉት ዓይነት ነው።

በቸር ይግጠምን

ጄኔቫ 09 May 2017

ማሳሰብያ: ይህ ጽሁፍ ከጥቂት ወራት በፊት “History: alkaline ….”በሚል አርዕስት በእንግሊዝኛ የጻፍኩትን አንዳንድ ጓዳኞቼ ካነበቡት በኋላ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ቢታተም ብዙ አንባቢዎች ሊኖሩት ይችላል ብለው ስለመከሩኝ ይህንን ይዘቱን ያልለቀቀ ግን ደግሞ አጠር ያለ ጽሁፍ በአማርኛ ለማቅረብ ወሰንኩ። መልካም የንባብ ጊዜ። (ባይሳ ዋቅ ወያ)

3 Responses to ታሪክ፦ የአለመግባባቶች መንስዔ ወይንስ መፍትሄ?

 1. ጎራው ምኒልክ አለም-አየሁ May 18, 2017 at 1:36 pm #

  Mengistu Hailemariam killed more Oromos than Menilik and Hailesselasie combined.

  Mengistu Hailemariam made sure Oromos do not practice their ancestoral religion ,while Hailesselasie himself was practicing Oromo’s ancestoral religion by going to Bishoftu to see his religious advisor named Mister Korit regualrly during the yearly IRECCHHA celebration time and other times of the year.

  Hailesselasie was 50% Oromo , 25% Gurage and 25 % Amara .Hailesselasie tried to incline more towards being Oromo in his personal free times. So if anything Oromos started geting kiled for being Oromo in Mengistu Hailemariam , Tamrat Layne , Meles Zenawi and Hailemariam Desalegn’s time.

 2. Boharsitu May 18, 2017 at 2:17 pm #

  https://www.theguardian.com/global-development/2017/may/16/uneasy-peace-ethiopia-three-flags-fly-oromia-somali-states-tension-ethnic-federalism

  Uneasy peace and simmering conflict in the town where three flags fly.

  Three different flags flutter in the breeze along the road that runs through Moyale in southern Ethiopia.

  The first is green, yellow and red: the colours of the Ethiopian federal state.

  Then, on the side of the road: red, black and white, with a tree in the centre, the colours of the Oromo.

  And a third: the green, white and red, with a camel in one corner, of Somali state.

  .Moyale, deep in Ethiopia’s dusty south-eastern drylands and straddling the border with Kenya, is split sharply down the middle. The fresh tarmac of the road that divides it marks the long-contested frontier between Oromia and Somali regional states.

  Analysis How long can Ethiopia’s state of emergency keep the lid on anger?
  A state crackdown has silenced ethnic Oromo people in Ethiopia, but grievances over land and rights, and a lack of political options, could reignite protests
  Read more
  These flags fly side-by-side in Moyale as a testament to the success of Ethiopia’s distinct model of ethnically based federalism, established in 1994.

  But it is also a measure of its failings: Moyale has two separate administrations; segregated schools; parallel court systems; rivalrous police forces, and adversarial local militia. More than 20 years after ethnic federalism was introduced, tensions between the two sides – Borana Oromo and Garri Somalis – are as fraught as ever.

  “.

  “Federalism brought this problem,” said Adam, the Igad officer. “People now think no one else can live in their area.”

  https://www.theguardian.com/global-development/2017/may/16/uneasy-peace-ethiopia-three-flags-fly-oromia-somali-states-tension-ethnic-federalism

 3. Kebe May 21, 2017 at 3:50 pm #

  I am writing this comment in English because my amharic type writing is too slow.

  I appreciated your article for bringing a different angle to look into our socities misunderstanding than the usual Minilik. It is good to have discussion to solve our problems. However, since the problems went on for so many years it has become so complicated and may not be so easy to solve it through mere discussion. To cite some of the problems:

  -Educational qualification starting from acceptance by the educational institutions to overriding exams and giving certificates that was given to Derge officials through direct order, such prvilage extended to party members and later to their children which has now become a deep rooted culture of favoring specific part of the society and using as a means to enslave the other part of the society. The same culture is observed in the employment, in the economic and other social activity. You may recall that Meles himself said that even a guard can be a government minister if he his a party member.

  – The favoritism towards members of the government party grew; to the extent of allowing lawlessness that the new generation has taken it as a norm that aggravated the theft and pilferage of the country resource and forced bribery of the society. 

  -The National love for the country has gone down to nearly nonexting and even among those who shade tears for unity, since it is known whose land and resource is being wasted. Therefore, it is hard to bring national sentiment in such environment.

  -There is no clear view or confusion on how Unity will work in this country. If unity to work, the government should have given their constitutional rights fully to the regions and shouldn”t have interfered. However, a one man dictatorship was installed instead which led to adopting all systems of the previous regimes and thereby bringing so much mess. If not superficial bit real unity is to be tried again , it can only be a confederation each having its own military and this may bringing responsible citizen at least to their own region.

Leave a Reply

Designed and Developed by NextGen IT Solutions