የ“አበበ በሶ በላ”ና “ጫላ ጩቤ ጨበጠ” ፖሊማኖታዊ አስተሳሰብ!

የ“አበበ በሶ በላ”ና “ጫላ ጩቤ ጨበጠ” ፖሊማኖታዊ አስተሳሰብ!

ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ, PH.D.*

ክፍል 3  

Previous ክፍል 1,  ክፍል 2 

(ማስታወሻ፡- ፖሊማኖታዊ የሚለው ቃል ‹ፖሊቲካዊና-ኅይማኖታዊ› የሚለውን ጽንሰ- ሐሳብ ይወክላል)

በኢትዮጵያ ፖሊቲካ ውስጥ ጐልቶ የሚታየውን ሁለት ጽንፈኛ አመለካከቶች እንዴት “ማስታረቅ” እንዳለብን ከዝህ በፊት በግልጽ ለማስቀመጥ ሞክረያለሁ። ከሁሉ በላይ፣ በአንድነት ኋይሎችና (ultra-right) በብሔርተኞች (ultra-left) መካከል ያለውን እልይ አስጨራሽ ፍልሚያን ማስታረቅ፣ አንድም ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ፣ አልያም ባለመስማማት ለመስማማት (agreeing to disagree) በጣም ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን በአጽንኦት አስምረበታለሁ። እነኝህን ጽንፈኛ አመለካከቶች በማስታረቅ ሂዴት ውስጥ ግን፣ አንድ አንድ እንከኖች ስያጋጥሙን “ምን ማድረግ አለብን?” የሚለው ጥያቄ መልስ የሚያስፈልገው አንገብጋብ ጉዳይ ይመስለኛል። በሌላ አገላለጽ፡- “በተለያየ ምክንያት በአንድነት ኋይሎችና በብሔርተኞች መካከል ያለውን የለየለት ልዩነት ማስታረቅ የማይፈልጉ አንዳንድ ግለሰቦች ሲያጋጥሙን፣ እንዴት ማስተናገድ ይኖርብናል?” የሚለው ነው።

አህምሮው ጤነኛ የሆነ ግለሰብ፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ዘላቂ ሠላም እንድሰፍን ከልብ ይመኛል፤ እንደ ዜጋም የራሱን አስተዋጾ ያበረክታል። የሕዝቡ ሠላም ማረጋገጥ የሚያስችሉ አሠራር እንድዘረጋ ደግሞ፣ የግለሰቦቹ አመለካከት (attitude) ወሳኝነት አለው። አንድ ማኅበረሰብ የአመለካከት ለውጥ ሳያደርግ የጋራ ግንዛቤ ላይ ፈጽሞ መድረስ አይችልም። ለምሳሌ፡- የተፈጥሮ ልዩነትን እንደ በታችነት ወይም እንደ በላይነት የሚረዳ ግለሰብ/ማኅበረሰብ፣ ለወንድና ለሴት ወይም ለነጭና ለጥቁር ሰው የሚሰጠው ክብር አንድ/እኩል ሊሆን አይችልም። “እኔ ወንድ አይደለሁም” ወይም “ጥቁር ገበያ” የሚለው አስተሳሰብ፣ የዝህ የተዛባ አመለካከት ውጤት መሆኑ በጣም ግልጽ ነው። ጉብዝናን ከወንድነት፣ ስርቆትን ከጥቁርነት ጋራ የሚያገናኝ መንስዔና-ወጤት (cause and effect) ላይ መድረስ ካልተቻለ፣ የአመለካከት ችግር አለ ማለት ነው። የአመለካከት ለውጥ ካልመጣ በስተቀር ደግሞ፣ አንድም በሴቶች ላይ የሚደርስ ጭቆና ማስቆም፣ አሊያም “ሌብነት ከነጮች ጋራ ሳይሆን ከጥቁሮቹ ጋራ ብቻ የተቆራኘ ነው” የሚል በጣም የተሳሳተ አረዳድ ፈጽሞ ማስቀረት አይቻልም። እንግድህ፣ የአመለካከት ለውጥ መጣ የሚንለው “ስርቆት ከቀለም ጋር፣ ጉብዝና ከጾታ ጋር ብቻ የተገናኘ ነው” የሚለውን የአስተሳሰብ ሽርሙጥና ማስቀረት ስንችል ብቻ ይሆናል ማለት ነው።

በሀገራችን ኢትዮጵያ የለየለት የአመለካከት ችግር ያለባቸው ሊሂቃን (በተለይ የፖሊቲካ መሪዎችና የኅይማኖት አባቶች) ያልነበሩበት ጊዜ አልነበረም። የወረደ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው እነኝህ ግለሰቦች፣ አንድን ግለሰብ/ቡድን አንድም ፍጹም እርኩስ፤ አሊያም ፍጹም ቅዱስ አድርጎ ያቀርባሉ። ለፍልስፍናዊ ትንተናችን መንደርደሪያ ይሆነን ዘንድ፣ ሰለሞን ስዩም “የኦሮሞ ጉዳይና የኢትዮጵያ ብያኔ፤ ከማሻሻያ፣ አመፃ እስከ አብዮት” በተሰኘ  መጽሐፉ ውስጥ ካሰፈረው ወስጥ የሚከተለውን ሐሳብ ወስደን ለአብነት እንመልከት፡-

በ2005 ዓ. ም የጥምቀት በአል አምቦ ከተማ እንዲህ ሆነ፤ ታቦቱ ወደ ማደርያ ሲመለስ በከተማዉ አንዱ መንገድ ላይ በአፋን ኦሮሞ፤ “Baga Ayaana Cuuphaa Nagahaan Geechan” (“እንኳን ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ” ማለት ነዉ) የሚል የመልካም ምኞት ፖስተር ተሰቅሎ ነበር። ታቦቱን ከተሸከሙት ቄስ አንዱ ቀጥ ብሎ ይቆማል፣ ግራ የተጋቡት አጃቢዎች ምን እንደ ሆነ ጠየቁት፣ ቀሱም “ይህንን የሰይጣን ቋንቋ ካላነሱ ታቦቱ አልሄድም ብሎኛል” ይላቸዋል። ቀሪዉ አይጠቅመንም፤ እዉነቱ ግን ይህን የመሰለ ዝቃጭ አስተሳሰብ የያዙ ዛሬም አሉ ነዉ። አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ትግሬ መስደብያ ቃላት ስያጥሩት “ጉሮሮ በሚፍቅ ቋንቋቸዉ” እንድል በ“አጤ ምንሊክ እና ኢትዮጵያ” መፅሀፉ። (ገጽ 56)

እንግድህ እኝህ “የተከበሩ” አባት “ኦሮሞና ሰይጣን የአንድ ሳንትም ሁለት ገጽታ መሆናቸዉን” መስክሮልናል። የ“መንፈስ ቅዱስ” ግልጠት መሆኑ ነዉ! ዓላማው “የሰለሞናዊ ሐረግ ፍልስፍና” ለማቀንቀን እንደ ነበር ግልጽ ነው!

እኔ የተወለድኩበት አካባቢ (ነቀምት/ወለጋ)፣ የአማርኛ ቋንቋ እንደ ጭራቅ እንድታይ ካደረጉት ብዙ ምክንያቶች አንዱ እንድህ አይነቱ ትምክህተኝነት ነው። ምክንያቱም፣ ትላንትም ሆነ ዛሬ፣ በአንዳንድ ግለሰቦች ዘንድ “ጫላ ጩቤ ጨበጠ” የሚለዉ ዐረፈተ-ነገር፣ “ጫላ በሶ በላ” በሚለዉ ዐረፍተ-ነገር ሊተካ አልቻለም። ስለዝህ፣ የሰይጣን ቋንቋ የሚጠቀም ጫላ፣ ጠብ አጫር ካልሆነ በስተቀር፣ እንደ “ሰለጠነው” አበበ በሶ መብላት አይችልም ብሎ የሚያስቡ ሰዎች አሉ። የሐጎስ፣ የጫላ፣ የሱገቦ፣የከበደ፣ የኦባንግ ወዘተ የማንነት ጥያቄ አንፃራዊ ምላሽ ካገኘ ከ25 ዓመታት ቦኋላ፣ ዛሬም የ“አበበ በሶ በላ”ና የ“ጫላ ጩቤ ጨበጠ” ፖሊማኖታዊ አስተሳሰብ አለመርገቡ ያስገርማል !!!

እና ምን ማድረግ አለብን? “የአመጽ ቋንቋ የአመጽን ቋንቋ ብቻ ነው የሚረዳ” የሚል ፍልስፍና መፍትሔ ያስገኝ ይሆን? አይመስለኝም! “የአማርኛ ቋንቋም የሰይጣን ቋንቋ ነው” የሚል ተመጣጣኝ ምላሽ የቅድሜ-ጥቅላሎት ሕፀፅ (fallacy of hasty generalization) እንድንፈጽም ያደርገናል። በሌላ አገላለጽ፣ ስለ አንድ ግለሰብ/ማኅበረሰብ ቀና አስተሳሰብ ያላቸው ብዙ ሰዎች ስላሉ፣ የአንድ ግለሰብ ወይም የጥቅት ሰዎች አመለካከት፣ የሁሉም ሰው እምነት ነው ማለት ፈጽሞ አይቻልም። በዝህ ሁኔታ፣ አንዱን ወገን ፍጹም እርኩስ፣ ሌላውን ደግሞ ፍጹም ቅዱስ አድርጎ ከመረዳት ይልቅ፣ “ጩቤና በሶ አበበንም ሆነ ጫላን ይመለከታል” የሚል ትክክለኛ አስተሳሰብ የሚከተሉ ሰዎች አሉ።

በበኩሌ፣ ምንም እንኳ የቁቤ ትውልድ (qubee generation) ቢሆንም፣ “የአማርኛ ቋንቋ የሰይጣን ቋንቋ ሳይሆን፣ በትክክል የሰዉ ልጅ ቋንቋ ነው” ብዬ በቅንነት መንፈስ ስላሰብኩ ብቻ በግል ጥረት ለመማር ችያለው። ያ ደግሞ በጣም ጠቅሞኛል፤ አንድም፣ ከብዙ ሰዎች ጋር እንድቀራረብና ከእነርሱም ብዙ ነገር እንድማር ብዙ የረዳኝ ሲሆን፣ ሁለትም ከብዙ የሥነ-ጹሑፍ ሥራዎች ጋር እንድተዋወቅ ምክንያት ሆኖኛል። የአማርኛ ቋንቋ መጻፍና ማንበብ ባልችል ኖሮ፣ የእኔ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር፣ ሎሬት ፀጋየ-ገብረመድህን፣መንግስቱ ለማ፣ በእውቀቱ ስዩም፣ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ ታገል ሰይፉ፣ እንዳለጌታ ከበደ፣ ማሞ ውድነህ፣ ሲሳይ ንጉሡ፣ መስፍን ሃብተማረያም፣ ገበየው አየለ፣ በዓሉ ግርማ፣ አዳም ረታ፣ ይስማእከ ወርቁ፣ ተስፋዬ ገ/አብ….ወዘተ ሥራዎች ሁሉ ቀርቶብኝ ነበር ማለት ነው!! አፋን ኦሮሞን (Afaan Oromo) ወይም የጉራግኛ ቋንቋን ወይም የግዕዝ ቋንቋን ወይም ደግሞ ማንኛውም ዓይነት ቋንቋ ባለመቻላቸው ብቻ ብዙ ነገር እንደቀረባቸው የሚያስቡ ግለሰበች ካሉ ቤት ይቁጠራቸዉ!

የሆነ ሆኖ፣ የዝህ “ቄስ” የቆሸሸ አስተሳሰብ አንድ የነቢይ መኮንን ግጥምን አስታወሰኝ፣

መች ይበጠስ ይሆን―ይህ የቂም ሰንሰለት?
ይህ የቂም ጉማሬ―ይሄ የቂም ኡደት
መች ይሆን አገሬ―ልጅ የምወጣላት
ቂም አርጅቶ ሞቶ―ሰዉ የሚኖርባት
በቀል ሬሳዉ ወጥቶ―ሰዉ የምንሆንባት!

ብሔራዊ መግባባት ላይ እነዳንደርስ እንቅፋት ከሚሆኑ ነገሮች አንዱና ዋነኛው እንድህ ዓይነቱ ንቀትና ጥላቻ ነው። ከማንኛውም ግለሰብ ፍጹምነት መጠበቅ ትክክል ባይሆንም፣ ፍደል ቆጥረናል የሚሉ የመንግስት ባለሥልጣናትና የኅይማኖት መሪዎች አንዳንድ ጊዜ ለምን እንደሚዘባርቁ ግልፅ አይደልም። የራስን የወረደ አስተሳሰብ በአደባባይ ማንፀባረቅ ከለየለት ድንቁርና የሚመነጭ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ስሳይ ንጉሡ “የቅናት ዛር” በተሰኘው ልቦለድ ሥራው “ቀፎ ጭንቅላቱ ትንሿን የግል ፍላጎቱን እንጂ የሚያወራው ነገር የሚያስከትለው አደጋ ሊያስብለት አልቻለም” (ገጽ 133) ያለው ነገር በትክክል የእነኝን ግለሰቦች ተግባር ይገልጻል የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ። ለነገሩ በሀገራችን ኢትዮጵያ የመንግስት ባለሥልጣን ወይም የኅይማኖት መሪ መሆን የሚታየው፣ ከሚያስከትለው ትልቅ ኅላፊነት አንፃር ሳይሆን፣ ከሚያስገኘው ጥቅምና ክብር አንፃር ብቻ አየሆነ መቷል። ፍልስፍና ለእንድህ ዓይነቱ የአስተሳሰብ ሽርሙጥና ፈጽሞ ቦታ የለውም!!

አብዛኛውን ጊዜ፣ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚንፀባረቀው የአመለካከት ልዩነት የበለጠ እንድለጠጥ የሚያረገው የብዙኅኑ ሕዝብ አስተሳሰብ ሳይሆን፣ የመንግስት ባለሥልጣናትና የኅይማኖት መሪዎች ድርግት ነው። እነኝህ ግለሰቦች ሕዝቡን በቅንነት መንፈስና በእኩልነት እንደሚመሩ ለት ተቀን ይሰብኩናል። ይሁን እንጅ፣ “የቀበሌ አስተሳሰብን” የሙጥኝ ብሎ እንኳን ሕዝብን ቤተሰብን መምራት አይቻልም። አንድ የኅይማኖት መሪ ወይም የመንግስት ባለሥልጣን ስለ ራሱም ሆነ ስለ ‹ሌላ›ው ወገን ያለውን የተሳሳተ አመለካከት ሳይቀይር ሕዝቡን በቅንነት አገለግላለው ብሎ “ቃል መግባት” ስበዛ ሌብነት ነው።

ብዙ ምሁራን ወይም የኅይማኖት መሪዎች በአንድ ሀገር ውስጥ ዘላቅ ሠላም እንድሰፍን ከተፈለገ፣ ሕዝቡ ምን ማድረግ እንዳለበት በምርምር ሥራዎቻቸው ውስጥ ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ። ተግባራቸው ግን ሌላ ነው። ለምሳሌ፡- ትናንት “የሰው ልጅ በሰውነቱ ብቻ መከበር አለበት” ሲል የነበረ አንድ “ምሁር” ወይም “የኅይማኖት መሪ”፣ የሚፈጸመውን ማንኛውም ዓይነት ኢ-ሰባአዊ ድርጊት በቀጥታ ከማውገዝ ይልቅ፣ 180 ድግሪ ተሽከርክሮ ተበዳዩ/ተጐጅው ከየትኛው ብሔር ወይም የየትኛው ኅይማኖት ተከታይ እንደሆነ ለማጣራት ጥረት ያደርጋል። “ክራይ ሰብሳብነት ፀረ-ዕድገት/ልማት ነው” የሚሉ ግለሰቦች፣ በአንድ ጀምበር የናጠጠ ሀብታም ይሆናሉ፤ ስያሰኛቸው ደግሞ ከአድስ አበባ ምሣ ተጋብዘው ለእራት ሎንደን ይከትማሉ…ወዘተ። ሆድና ህልና በተሰማሙበት ማኅበረሰብ ውስጥ እውነተኛ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት በጣም አስቸጋር ይመስለኛል።

ያም ሆነ ይህ፣ በሀገራችን ውስጥ የሚታየውን ማንኛውም ዓይነት ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት ትክክለኛው መንገድ አስቀድሞ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት እንደሆነ ይህ ጸሐፊ በአጽንኦት ያሰምርበታል። ተወደደም ተጠላ፣ በአንድነት ኋይሎችና በብሔርተኞች መካከል ያለውን የለየለት የአመለካከት ልዩነት ማጥበብ የሚቻለው፣ የምዕራቡን ዓለም ፖሊቲካዊ ፍልስፍና በትክክል ስንረዳ ብቻ ይሆናል።

  • በአንድ በኩል፣ “ብሔራዊ ስምምነት ላይ መድረስ የሚንችለው አንድ ወጥ አመለካከት/ማንነት ስኖር ብቻ ነው” የሚል እምነት ስበዛ ግልብ አስተሳሰብ ይመስለኛል። አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሀገር፣ አንድ ኅይማኖት ያላት ሶማሊያ እንኳ ለዝህ አልታደለችም። ለምሳሌ፡- በንገሡ ዘመን የኢትዮጵያ የትምህርት ሚንስቴር ሚኒስትር የነበሩት ሣህሌ ፀዳሉ፣ በ1933 የሚከተለውን በጣም የተሳሳተ አዋጅ አሳውጀው ነበሩ፡- “ያገር ጉልበት አንድነት ነው፣ አንድነትንም የሚወልደው ቋንቋ ልማድና ሃይማኖት ነው። ስለዝህ ኢትዮጵያ ቀዳማዊ መሆኗን ለማስከበር አንድነቷንም ለማጽናት እስከሁን በቆየው ልማዳችን ተማሪ ቤቶቻችንን አስፍተን ቋንቋችንና ሃይማኖታችንን በመላው በኢትዮጵያ ግዛት በአዋጅ እንዘርጋው፤ ይህ ካልሆነ እስከ መቼውም ድረስ አንድነት አይገኝም። በመላ በኢትዮጵያ ግዛት ለሥጋዊና ለመንፈሣዊ ሥራ ያማርኛና የግዕዝ ቋንቋ ብቻ በሕግ ጸንተው እንዲኖሩ ሌላው ማናቸውም የአረማዊያን ቋንቋ ሁሉ እንዲደመሰስ ማድረግ ያስፈልጋል።…ሚሲዮኖች ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎችንም ቢሆን እንዳይከፍቱ መከልከል ያስፈልጋል፤ ከከፈቱም የውጪ ቋንቋ ማስተማርም ቢሆን እድሉ ለኢትዮጵያውያን መሰጠት አለበት።” (ባህሩ ዘውዴ 2005፡ 132-141) “ማንነቴን የማትቀበል ኢትዮጵያ 99 ቦታ ትበጣጠስ” የሚሉ ግለሰቦች እብድ ስለሆኑ ሳይሆን፣ እንድህ ዓይነቱን ጸረ-ሰው ልጅ መብት አዋጅ ፈጽሞ ስለማይቀበሉ ብቻ ነው!
  • በሌላ በኩል፣ “የራስን ዕድል በራስ መወሰን” የሚለው ነገር፣ በአፊሪካ ቀንድ ዘላቂ ሠላም ያሰፍናል ብሎ መደምደም፣ የምዕራቡን ዓለም ፖሊቲካዊ ፍልስፍና በትክክል አለመገንዘብን ያመለክታል። እዝ ላይ እንደ አንድ ዜጋ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድን እውነታ በድፍረትና በግልፅ ለማስረዳት ይወዳለው፤ አሁን በሕግ-መንግስቱ ላይ በግልፅ የሰፈረው አንቀጽ 39 በኢትዮጵያ ምድር ብተገበር እንኳ፣ኢትዮጵያ በሚትባል ሀገር ውስጥ ዘላቂ ሰላም ይሰፍናል ብሎ ማሰብ፣ ከ2ኛው የዓለም-ጦርነት ወድህ ምዕራቡ ዓለም በአፊሪካ/በኢትዮጵያ ውስጥ የዘረጋውን የእጅ አዙር ቅኝ-ግዛትን በሚገባ ያለማጠንን ያሳያል። የበለጠ ግልጽ ለማድረግ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድም ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ፣ ሁለትም ባለመስማማት ለመስማማት (agreeing to disagree) የሚለው ነገር በራሱ ዋጋ አይኖረውም። ይልቅ፣ አፊሪካ/ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላትን የዕድገት ፖሊስ እንደገና ማጠን  ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ጉዳይ ነው። ብዙ ምሁራን (አፊሪካዊያን/ኢትዮጵያዊያን) ይህንን እውነታ አያውቁም ማለት አይቻልም። የኢትሮፕያንስ (Westernized Ethiopians) ዋነኛ ችግር፣ የኢትዮጵያ ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት፣ የምዕራቡን ዓለም የዕድገት ሞደል የመከተላቸው ጉዳይ ነው። ለምሳሌ፡- የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ኢህአዴግ አብዮታዊ ድሞክራስን መከተሉ ‹ትክክል› ነው። ይሁን እንጅ፣ ኢህአዴግ ከሕገ-መንግስቱ ይልቅ ኢትሮፕያንስን አብዝቶ ስለምሰማ፣ በአፈጻጸም ላይ ከፍተኛ ችግር እየገጠመው ነው። ያም ሆነ ይህ፣ ሙስና ለምሉት ካንሰር መፍትሔው ምን እንደሆነ ወይም ያለብንን የውጭ እዳ መቼ ከፍለን እንደምንጨርስ የሚያውቁት ፈጣሪና ኢህአዴግ ብቻ ናቸው!!!

በአጠቃላይ፣ ከዝህ በፊት በግልፅ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት፣ የተማረ ክፍል የኢትዮጵያን/የአፊሪካን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ጥቅሞችን ከማስጠበቅ ይልቅ፣ ለብዝበዛ አሳልፎ በመስጠት አፊሪካ/ኢትዮጵያ በእጅ አዙር ቅኝ-አገዛዝ ስር እንድትማቀቅ ያደረጉ ናቸው። አመለኛን ወይፈን ጨው እያላስን አንገቱ ላይ ገመድ እንደምናስርበት ሁሉ፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ / የአፊሪካ ምሁራን ምዕራቡ ዓለም በራሱ ቁመት ለክቶና ቆርጦ በሰፋው የአኮኖሚና የፖሎቲካ ፖሊስ ሰተት ብሎ በመግባት፣ ምዕራባዊያን ገቶቻቸውን ማገልግል ቀጥሎበታል። የራሳቸውን ታሪክ/ሥርዓት ትተው ቅኝ-ገዥዎች ትቶላቸው የሄዱትን አሰራር/ታሪክ መከተል ስለጀመሩ፣ የሰፍውን ሕዝብ ጥቅም ለግላቸው በማድረግ አህጉርቷን እየበዘበዙ ይገኛሉ። እንደዝህ ዓይነቱን አሠራር ተከትለን፣ በአፍሪካ አህጉር ዉስጥ ዘላቅ ሰላም ይሰፍናል አልያም አስተማማኝ የኢኮኖሚ እድገት ይኖራል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። የኢትዮጵያ ዕጣ-ፈንታም ከዝህ የተለየ አይደለም!

በበኩሌ፣ አበበ በሶ በላጫላ ጩቤ ጨበጠፖሊማኖታዊ አስተሳሰብ ፈተናን አንድ ቀን እናልፋለን የሚል ተስፋ ቢኖረኝም፣ ዶላርነትምክንያት ግን ይህ የሚሳከ አይመስለኝም። “The modern [contemporary] 20th [21st] centurey weapon of neo-imperialism is ‘dollarism’” Malcom X. ስለዝህ አካሄዳችን ተስፈ የሚያስቆርጥ ሆኖ አግንቸዋለሁ። ‹‹ያ ትውልድ›› ካለፈው ጥፋቱ ተምሮ፣ ልዩነቱን አቻችሎና አንድነቱን ጠብቆ ኢትዮጵያን ከመበታተን ይታደጋት ይሆን? ጊዜ የሚነግረን ይሆናል!

ምንጭ፡- ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ፣ የኢትዮሮፒያንስ የአስተሳሰብ ቅሬ፣ ገጽ. 41-46-49

ቸር እንሰንብት!    

 

No comments yet.

Leave a Reply